Ezekiel 28

በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለጢሮስ ገዥ እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ልብህ በትዕቢት ተወጥሮ፣
“እኔ አምላክ ነኝ፤
በአምላክ ዙፋን ላይ፣
በባሕሮችም ልብ ተቀምጫለሁ” አልህ።
ምንም እንኳ እንደ አምላክ ጠቢብ ነኝ ብለህ ብታስብም፣
አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።
3ከዳንኤል
ወይም ዳኔል፤ የዕብራይስጡን ቃል አጻጻፍ ስንመለከት ነቢዩ ዳንኤልን ሳይሆን ሌላን ሰው የሚያመለክት ነው።
ይልቅ ጠቢብ ነህን?
ከአንተስ የተሰወረ ምስጢር የለምን?
4በጥበብህና በማስተዋልህ፣
የራስህን ሀብት አከማቸህ፤
ወርቅም ብርም፣
በግምጃ ቤትህ አጠራቀምህ።
5በንግድ ሥራ እጅግ ከመራቀቅህ የተነሣ፣
በሀብት ላይ ሀብት አካበትህ፤
ከሀብትህ ብዛት የተነሣም፤
ልብህ በትዕቢት ተወጠረ።
6“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘እንደ አምላክ ጥበበኛ ነኝ፤ ብለህ
ስለምታስብ፣
7ከአሕዛብ መካከል እጅግ ጨካኞች የሆኑትን ባዕዳን፣
በአንተ ላይ አመጣለሁ፤
በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ፤
ታላቅ ክብርህንም ያረክሳሉ።
8ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤
በጥልቁም ባሕር ውስጥ፣
በባሕሮችም ልብ ውስጥ አስከፊ ሞት ትሞታለህ።
9ታዲያ በገዳዮችህ ፊት፣
“አምላክ ነኝ” ትላለህን?
በገዳዮችህ እጅ ስትገባ፣
አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።
10በባዕዳን እጅ፣
ያልተገረዙትን ሰዎች አሟሟት ትሞታለህ፤
እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

11 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 12“የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ጢሮስ ንጉሥ ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ጥበብን የተሞላህ፣ ፍጹም ውበትን የተላበስህ፣
የፍጹምነት ምሳሌ ነበርህ።
13በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ፣
በዔድን
ወይም ላፒስ ላዙሊ
ነበርህ፤
እያንዳንዱ የከበረ ድንጋይ አስጊጦህ ነበር፤
ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ አልማዝ፣
መረግድ፣ ኢያሰጲድ፣ ሰንፔር፣
በሉር፣ ቢረሌና የከበረ ዕንቍ።
ከእነዚህ የከበሩ ድንጋዮች መካከል አንዳንዶቹ ትክክለኛ ማንነታቸው ተለይቶ አይታወቅም

ልብስህም የሚያብረቀርቅ ዕንወርቅ ነበር፤
የተዘጋጁትም አንተ በተፈጠርህበት ዕለት ነበር።
14ጠባቂ ኪሩብ ሆነህ ተቀብተህ ነበር፤
ለዚሁም ሾምሁህ፤
በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ነበርህ፤
በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ።
15ከተፈጠርህበት ቀን ጀምሮ፣
ክፋት እስከ ተገኘብህ ድረስ፣
በመንገድህ ነቀፌታ አልነበረብህም።
16ንግድህ ስለ ደረጀ፣
በዐመፅ ተሞላህ፣
ኀጢአትም ሠራህ፤
ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ በውርደት አሳደድሁህ፤
ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፤ ከእሳት ድንጋዮች
መካከል አስወጣሁህ።
17በውበትህ ምክንያት፣
ልብህ ታበየ፤
ከክብርህ ታላቅነት የተነሣም፣
ጥበብህን አረከስህ።
ስለዚህ ወደ ምድር ወረወርሁህ፤
ለነገሥታት ትዕይንት አደረግሁህ።
18በኀጢአትህና በተጭበረበረው ንግድህ ብዛት፣
መቅደስህን አረከስህ።
ስለዚህ እሳት ከአንተ እንዲወጣ አደረግሁ፤
እርሱም በላህ፤
በሚመለከቱህ ሁሉ ፊት፣
በምድር ላይ ዐመድ አደረግሁህ።
19የሚያውቁህን አሕዛብ ሁሉ፣
ሁኔታህ አስደንግጧቸዋል፤
መጨረሻህ የሚያሳዝን ሆነ፤
ከእንግዲህ ህልውና የለህም።’ ”

በሲዶን ላይ የተነገረ ትንቢት

20 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 21“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ሲዶና አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባት፤ 22እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ሲዶን ሆይ፤ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤
በውስጥሽ እከብራለሁ፤
ቅጣትን ሳመጣባት፣
ቅድስናዬንም በውስጧ ስገልጥ፣
እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23በእርሷ ላይ መቅሠፍት አመጣለሁ፤
በመንገዶቿ ላይ ደም እንዲፈስስ አደርጋለሁ፤
ከየአቅጣጫው በሚመጣ ሰይፍ፣
የታረዱት በውስጧ ይወድቃሉ፤
ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
24“ ‘ከእንግዲህ ወዲያ የእስራኤል ሕዝብ የሚያሠቃይ አሜከላና የሚወጋ እሾኽ የሆኑ ጎረቤቶች አይኖሯቸውም፤ ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።

25“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው። 26በዚያም በሰላም ይኖራሉ፤ ቤቶች ይሠራሉ፤ የወይን ተክል ቦታም ያበጃሉ። ያጣጣሏቸው ጎረቤቶቻቸውን ሁሉ በምቀጣበት ጊዜ እነርሱ በሰላም ይኖራሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

Copyright information for AmhNASV